1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፦ሚያዚያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም.

Hirut Melesseሐሙስ፣ ሚያዝያ 24 2016

የሚያዚያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የላስታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው መልሴና የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን አፈወርቅ እንዲሁም የራያ አላማጣ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞላ ደርበው ሰሞኑን በታጣቂዎች ተግደለዋል ሲሉ ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ገልጸዋል። የጋዛው ጦርነት ጦርነቱ ዛሬ ቢቆም እንኳን የወደሙትን ቤቶች መልሶ ለመገንባት ቢያንስ 16 ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል የተመድ አስታወቀ። የአውሮጳ ኅብረት ለሊባኖስ አንድ ቢሊዮን ዩሮ ወይም 1.07 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የፋይናናስ እርዳታ ለመስጠት ቃል ገባ።

https://p.dw.com/p/4fRSC

ባህር ዳር ሦስት የአማራ ክልል ባለሥልጣናት መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ሦስትየአማራ ክልል ባለሥልጣናት ሰሞኑን በታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ተናገሩ። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የላስታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው መልሴና የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን አፈወርቅ መንገድ ላይ ባደፈጡ ታጠቂዎች ባለፈው ማክሰኞ መገደላቸውን ሁለት የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ባለስልጣናቱ የተገደሉት ወልዲያ ከተማ ስብሰባ ሰንብተው ሲመለሱ ገነተ ማሪያምና ኩል መስክ በተባሉ አካባቢዎች መካከል ነው። ስለጥቃት አድራሾቹ ማንነት አስተያየት ሰጪዎቹ ያሉት ነገር የለም። በተመሳሳይ ሁኔታ የራያ አላማጣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞላ ደርበው ሰሞኑን በአካባቢ የሚደረገዉን ግጭት ሸሽተዉ ወደ ቆቦ ከተማ ለመጓዝ ሲሞክሩ መገደላቸውን አንድ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ ለዶይቸ ቬሌ ገልጠዋል።ዶቼቬለ ስለ ሦስቱ ሰዎች ግድያዎች ከሚመለከታቸው የየአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት ማረጋገጫ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ።

ሀዋሳ የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገላቸው

የደቡብ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥታት የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ 2 ሺህ 381 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረጉ። ይቅርታ ከተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች መካከል 1 ሺህ 455ቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ቀሪዎቹ 926 ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የነበሩ ናቸው። ለተራሚዎቹ ይቅርታው የተደረገው በየክልሎቹ በሚገኙ የይቅርታ ቦርዶች አማካኝነት ለክልል መንግሥታቱ ቀርቦ ይሁንታን በማግኘቱ ነው ተብሏል ። ይቅርታው ተግባራዊ የተደረገው በይቅርታ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ መሠረት መስፈርቱን የሚያሟሉ ታራሚዎችን በመለየት መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ሃላፊ አቶ እሸቱ ጎዴቶ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡ዛሬ ወደ ማህበረሰቡ የተቀላቀሉት ታራሚዎች ወደፊት ሰላማዊ ኑሮ ለመምራት የሚያስችላቸው የሥነ ልቦና ምክር እንደተሰጣቸውም የቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል

ናይሮቢ ኬንያ ሴት የአየር ኃይል አዛዥ ሾመች

ኬንያ ሴት የአየር ኃይል አዛዥ ሾመች። የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቲ ዛሬ በሰጡት ሹመት ሜጀር ጀነራል ፋጡማ ጋቲ አህመድን የኬንያ አየር ኃይል አዛዥ አድርገው ሾመዋል። ፋጡማ ጋቲ አህመድ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የአየር ኃይል አዛዥ ናቸው። የተኩትም የቀድሞውን የአየር ኃይል አዛዥ ጆን ሙግራቪ ኢትየኖን ነው። ኢትየኖን በአዲሱ ሹመት ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ሆነዋል። በቅርቡ በደረሰ የሄሊኮፕተር አደጋ በሞቱት በመከላከያ ሚኒስትሩ በፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላ ምትክም ቻርልስ ሙሪዩ ካሃሪን በመከላከያ ሚኒስትርነት ሾመዋል።ካሃሪ የሟቹ የኦጎላ ምክትል ነበሩ።

ብራሰልስ የአውሮጳ ኅብረት ለሊባኖስ 1.07 ቢሊዮን ዶላር ሊሰጥ ነው

የአውሮጳ ኅብረት ለሊባኖስ አንድ ቢሊዮን ዩሮ ወይም 1.07 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የፋይናናስ እርዳታ ለመስጠት ቃል ገባ ።ኅብረቱን እርዳታውን ለሊባኖስ የሚሰጠው በሀገርዋ የሚገኙ ሶሪያውያን ስደተኞችን ወደ አውሮፓ ኅብረት እንዳይመጡ እንድታስቆም ነው። የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ዛሬ ሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ ከሊባኖስ ባለ አደራ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲና ከቆጵሮስ ፕሬዝዳንት ኒኮስ ክሪስቶዱሊዲስ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ እንዳስታወቁት፣ የገንዘብ ማዕቀፉ ከያዝነው 2024 ዓም አንስቶ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2027 ድረስ የሚሰጥ ነው። የአውሮጳ ኅብረት ፍላጎትም ሀገሪቱን በተለይ በማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ዘርፎች መደገፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

«ለሊባኖስ ማኅበራዊ-ኤኮኖሚ መረጋጋት አስተዋጽኦ ማድረግ እንፈልጋለን።በመጀመሪያ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ፣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን በማጠናከር ለምሳሌ በትምሕርት ወይም በማኅበራዊ ጥበቃዎች በሊባኖስ ህዝብ ጤና አጠባበቅ ላይ ያተኮሩ ውረታዎች እንዲጠናከሩ እንፈልጋለን። ሁለተኛ የኤኮኖሚ የፋይናናስ እና የባንክ ስራ ማሻሻያዎችን ስታካሂዱ ከጎናችሁ እንሆናለን። »

የእርዳታ ማዕቀፉ ከሊባኖስ ትምሕርትና ከማኅበራዊ ጥበቃ በተጨማሪ ለጦር ኃይሉ ድጋፍም ይውላል ተብሏል ። ለጦር ኃይሉ የሚሰጠው ድጋፍም በዋነኛነት ለቁሳቁስ አቅርቦትና ስልጠና እንዲሁም ድንበር ላይ ለሚያስፈልግ መሠረተ ልማት አስተዳደርም ይውላል ብለዋል። የሊባኖስ ባለአደራ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚካቲ በበኩላቸው ሀገራቸውን ለሶሪያ ስደተኞች እንደምትክ ሀገር አድርጎ መውሰድን እንደሚቃወሙ ገልጸው ከሶሪያ ግዛት አብዛኛዎቹ ደኅንነታቸው የተጠበቀ በመሆኑተፈናቃዮች የሚመለሱበትን ሂደት የሚያመቻች መሆኑ አውሮጳዊ እና ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንዲሰጠው መስማማታቸውንም ገልጸዋል። ሊባኖስ በአሁኑ ጊዜ የተመድ የመዘገባቸውን 805 ሺህ የሶሪያ ስደተኞችን አስጠግታለች። የሊባኖስ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በሀገሪቱ የሚገኙት ሶርያውያን ስደተኞች ቁጥር ከ1.5 ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ይደርሳል።

የተመድ በጋዛው ጦርነት የወደሙ ቤቶች መልሶ ለመገንባት ቢያንስ 16 ዓመታት ይፈጃል

በጋዛው ጦርነት የወደሙትን ቤቶች መልሶ ለመገንባት ቢያንስ 16 ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል የተመድ አስታወቀ። የተመ የልማት መርሀ ግብር ዛሬ ይፋ ባደረገው ግምቱ ጦርነቱ ዛሬ ቢቆም እንኳን በ7 ወራት ውስጥ በእስራኤል የጋዛ የምድርና የአየር ድብደባ የወደመውን መልሶ ለመገንባት እስከ ጎርጎሮሳዊው 2040 ድረስ ሊወስድ ይችላል ብሏል። የድርጅቱ አስተዳዳሪ አሺም ሽታይነር በጋዛ ጉዳት የደረሰባቸው ቤቶች ቁጥር ቢያንስ 370 ሺህ እንደሚሆን ገልጸው ከመካከላቸው 79 ሺሁ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል እና ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ዩናይትድ ስቴትስ ግፊትዋን አጠናክራለች። የሀማስ-እስራኤል ጦርነት ከተጀመረው ወዲህ ለሰባተኛ ጊዜ ወደ አካባቢው የሄዱት የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ሀማስ ከእስራኤል ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጊያው ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ወደ ጋዛ የሚገባው እርዳታ መጠን እንዲጨምርም እስራኤልን ጠይቀዋል። ለሁለቱ ወገኖች በቀረበው የአሁኑ የተኩስ አቁም እቅድ ጦርነቱ ሲቆም ሀማስ ከ7 ወራት በፊት ያገታቸውን እስራኤላውያን እንዲለቅ በምትኩም ለጋዛ የሚያስፈልገው ምግብ መድኃኒትና ውሀ እንዲገባ እንዲሁም እስራኤል የያዘቻቸውን ፍልስጤማውያን እንድትፈታ ይጠይቃል። የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት እንደሚሉት ባለፉት 24 ሰዓታት በእስራኤል የአየር ጥቃት 28 ሰዎች ተገድለዋል። በ7 ወራቱ ጦርነት የሞቱት ቁጥር ከ34 ሺህ 500 ፍልስጤማውያን በላይ መሆኑን በጋዛው ጦርነት የተፈናቀሉት ደግሞ ከህዝቡ ወደ 80 በመቶ ወይም 2.3 ሚሊዮን እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

በርሊን ኢማኑኤል ማክሮ ጀርመንን በይፋ ሊጎበኙ ነው

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ግንቦት አጋማሽ ላይ በጀርመን የሦስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የጀርመን ፕሬዝዳንታዊ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ጽህፈት ቤቱ እንዳለውው ማክሮንና ባለቤታቸው ብርጊተ ማሪ ክሎድ ማክሮን በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 26 ቀን 2024 ዓ.ም. በርሊን ሲደርሱ በጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርና በባለቤታቸው በኤልከ ቡደንቤንደር፣ በቤልቪዩ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት በሙሉ ወታደራዊ ክብር አቀባበል ይደርግላቸዋል። ማክሮን በግንቦቱ ጉብኝታቸው በርሊን በሚገኘው የጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ በሚከበረው የጀርመን ሕገ መንግሥት 75ተኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ይገኛሉ። ማክሮን ከበርሊን በተጨማሪ በድሬስደንና በሙንስተር ከተሞችም ጉብኝት ያደርጋሉ። በተለይ በድሬስደኑ ጉብኝታቸው ከዚህ ቀደም በታቀደው መሠረት አውሮፓን የተመለከተ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከጎርጎሮሳዊው 2000 ዓ.ም. ወዲህ አንድ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት በጀርመን ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርግ የግንቦቱ የማክሮን ጉብኝት የመጀመሪያው ይሆናል ተብሏል። በ2000 ዓም ጀርመንን በይፋ የጎበኙት የያኔው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ዣክ ሺራክ ነበሩ። የግንቦቱ የማክሮን ጉብኝት ለባለፈው ዓመት ሐምሌ ነበር የታቀደው። ሆኖም በወቅቱ የ17 ዓመቱ ወጣት ናሄል ሜርዞክ በፈረንሳይ ፖሊስ ከተገደለ በኋላ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ የያኔው ጉብኝት ተሰርዞ አዲስ የጉብኝት ቀን ተይዟል።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።