1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2016

https://p.dw.com/p/4fN3U

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመንገዶኞች መጓጓዣ ባቡር ቢኬ የተባለ ጣቢያ ላይ በመቆሙ መንገላታታቸውን ተሳፋሪዎች ለዶይቸ ቬለ በስልክ ተናገሩ።

"በባቡሩ ቀጣይ መድረሻ ጣቢያ ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች ከጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ጋር በተያያዘ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ለባቡሩ ከጉዞ መገታት ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የተገለጸው ።

ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ቢኬ በተባለው ጣቢያ እንደቆሙ መሆናቸውን የተናገሩት መንገደኛ በዚህም መንገላታታቸውን ገልፀው እስካሁንም ምንም ዓይነት ትክክለኛ መረጃ አለማግኘታቸውን ገልፀዋል።

« ከድሬደዋ የተነሳነው ልክ ሁለት ሰዓት ሲል ነው ። ከዚያ ለአንድ ሰዓት ያህል ተጉዘን የቢኬ ስቴሽን ላይ ቆመ።ያ ማለት ሶስት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ አካባቢ ማለት ነው።ከዚያ በኃላ እስከ አሁን ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አለን እዛው ቆመናል።»

የድሬዳዋው ወኪላችን መሳይ ተክሉ በተፈጠረው ሁኔታ ላይ የኮርፖሬሽኑን የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ጠይቆ በሰጡት ምላሽ የተሟላ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። ነገር ግን "የመንገዱን ደህንነት ለማረጋገጥ ከዋናው የህዝብ ማጓጓዣ ባቡር ቀደም ብሎ የሚወጣው የፍተሻ ባቡር ለሁለት ሰዓት ያህል መዘግየቱን ከቴክኒክ ክፍል መስማታቸውን" ተናግረዋል ።

«ቴክኒካል ዲፓርትመንት ስራውን ከሚመሩት የሰማሁት የሁልት ሰዓት መዘግየት /ዲሌያንስ እንደነበር ነው ስጠይቅ የሰማሁት። ከአንድ የህዝብ ማጓጓዣ ባቡር ከመውጣቱ በፊት መንገድ ላይ የመስመሩን ደህንነት ለማረጋገጥ ቀድሞ የሚወጣ ባቡር አለ እሱ ለሁለት ሰዓት ያህል መዘግየት ነበረው። »

ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት እስከ አስር ሰዓት ድረስ ጠዋት ሶስት ሰዓት ግድም ከድሬደዋ ብዙም ሳይርቅ ጉዞውን ያቋረጠው የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ማጓጓዣ ባቡር ከቢኬ አለመንቀሳቀሱ ታውቋል።

የኬንያ የህይወት አድን ሰራተኞች በጎርፍ ተጠርገው የተወሰዱ 91 ሰዎችን ለማግኘት ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለ46 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው እና በማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ ትናንት ሰኞ አንድ ግድብ ከደረመሰ በኋላ ነው።

በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በምትገኘው የማይ ማሂዩ ከተማ አቅራቢያ የደረሰው የግድብ መደርመስ ቤቶችን ጨምሮ በጎዳና ላይ ያገኛቸውን ተሽከርካሪዎች ጠራርጎ ወስዷል ነው የተባለው። ኬንያ ኤል ኒኖ ባስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ 170 ያህል ዜጎቿን በሞት ተነጥቃለች፤ ከ185 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ መኖሪያ አልባ ሆነዋል።ይህንኑ ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ካቢኔያቸውን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል። ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ከ50 በላይ መንደሮችን እንዳልነበር ካደረገውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ማገገም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉም ተብሏል። በኬንያ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ኃይለኛ ዝናብ ቀጣዮቹን ቀናት ሊጥል እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ ።

ዩናይትድ ስቴትስ ሃገራት ለሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የጦር መሳሪያ ከማቅረብ እንዲታቀቡ አስጠነቀቀች።

አሜሪካ ማስጠንቀቂያውን የሰነዘረችው በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር ያለው ከ20 ዓመታት በፊት የተከሰተው አይነት «የዘር ማጥፋት» ራሱን ሊደግም የሚችልበት አዝማሚያ መታየቱን ተከትሎ ነው። በመንግስታቱ ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በዝግ ከተካሄደው የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ ለጋዜጠኞች እንዳሉት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የምትገኘው የዳርፉሯ ኤል ፋሽር «የጅምላ ፍጅት አፋፍ » ላይ ናት ። አምባሳደሯ በማሳሰቢያቸው « የከፋ ቀውስ» ከመስተናገዱ አስቀድሞ ሁሉም ወገኖች የጦር መሳሪያ ወደ ሱዳን መላክ ማቆም አለባቸው ብለዋል።

ደረሰን ያሉትን ታማኝ መረጃ የጠቀሱት አምባሳደሯ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና አጋር ሚሊሻዎች ባደረሱት ጥቃት ከኤል ፋሽር በስተምዕራብ የሚገኙ በርካታ መንደሮችን አውድመዋል። ጥቃቱን ተከትሎ 2 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ጨምሮ ከ500 ሺ በላይ ተፈናቃዮችን የያዘችው አልፋሽር አደጋ ተደቅኖባታል ።

የብሪታንያ ምክትል አምባሳደር ጀምስ ካሪዩኪ በበኩላቸው «ሱዳን የሚያስፈልጋት የመጨረሻው ነገር ከዚህ ዓመቱ ግጭት የከፋ ተጨማሪ ቀውስ እንዳታስተናግድ ነው።» ብለዋል። ከሁለት አስርት አመታት በፊት በምዕራብ ዳርፉር በጃንጃዊድ የአረብ ሚሊሻዎች በፈጸሟቸው የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የማዕከላዊ ወይም የምስራቅ አፍሪቃ ጎሳ አባላት የሆኑ ከ300 ሺ በላይ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

የእስራኤል ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ባደረሰው ጥቃት 47 ተጨማሪ ፍልስጥኤማውያን ተገደሉ፤ ሌሎች 61 ቆሰሉ ።

በጋዛ ሰርጥ በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተገደሉ ፍልስጥኤማውያን ቁጥር 34,535 መድረሱን የጋዛ የጤና ሚኒስቱር አስታውቋል። ከ77 ሺ በላይ ፍልስጥኤማውያን ቆስለዋል።

የእስራኤል ጦር በአየር ጥቃት ባወደማቸው የህንጻ ፍርስራሾች ስር ከ10 ሺ በላይ ፍስጥኤማውያን ተቀብረው እንደሚገኙ የጋዛ የአስቸኳይ ጊዜ የሲቪል አገልግሎት አስታውቋል። የፈራረሱ ህንጻዎች ህንጻዎችን በማስወገድ የሰዎች አስክሬን ለማንሳት የግዙፍ ማሽነሪዎች እጥረት እንደገጠመው የገለጸው አገልግሎቱ አስክሬኖች በወቅቱ ባለመቀበራቸው ለበሽታዎች መዛመት ምክንያት እየሆኑ ነው ብሏል። የበጋ ወቅት መምጣት እና የሙቀት መጨመር ችግሩን የከፋ እንዳያደርገው አስግቶኛልም ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለቱ ተቀናቃኝ የፍልስጥኤማውያን ቡድኖች ሃማስ እና ፋታህ በንግግር እርቅ ለማውረድ ፖለቲካዊ ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ። ሁለቱ ቡድኖች ለፊት ለፊት ንግግር ከጥቂት ቀናት በፊት ቤጂንግ መግባታቸውን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዛሬ አስታውቋል። ሃማስ ፋታህን ከጋዛ ሰርጥ ካስወገደበት ከጎርጎርሳውያኑ 2007 ወዲህ ሁለቱ ፍልስጥኤማውያን ተቀናቃኝ ቡድኖች የሰመረ የፖለቲካ ንግግር አካሂደው አያውቁም ። የአሁኑ የፊት ለፊት ንግግር ምናልባትም እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ያደረሰችው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ተከትሎ የመጣ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመለክተው።

የፍልስጥኤምን አንድነት በሚያረጋግጥ መልኩ ውይይታቸውን ለመቀጠል ሁለቱም ወገኖች ከስምምነት መድረሳቸውን የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትቴር ቃል አቃባይ ሊን ጂያን ተናግረዋል። ቻይና ሁለቱን ቡድኖች በአንድ ጠረጴዛ ዙርያ በማቅረቧ ከሁለቱም ወገኖች ምስጋና ተችሯታል።

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።