1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበራት ኮንፌደሬሽን ጥሪ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2016

ሚያዝያ 23 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን ከአደባባይ ይልቅ አዳራሽ ውስጥ በሚደረግ ውይይት ተከብሮ እንዲውል መወሰኑን ኢሰማኮ አስታወቀ። ሠራተኞች የሕይወት፣ የአካል፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳቶች ሰለባነታቸው በፊት በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ በሰፋው ጦርነት ፣ አሁን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ጎልቶ መታየቱን ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4fLzi
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበራት ኮንፌደሬሽን
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበራት ኮንፌደሬሽንምስል CETU

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበራት ኮንፌደሬሽን ጥሪ

የሠራተኞች ቀን - ሜይ ዴይ

ነገ ሚያዝያ 23 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን ከአደባባይ ይልቅ አዳራሽ ውስጥ በሚደረግ ውይይት ተከብሮ እንዲውል መወሰኑን የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበራት ኮንፌደሬሽን ( ኢሰማኮ ) አስታወቀ። ክብረ በዓሉ በአዲስ አበባ እና ሌሌች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ባሉባቸው ከተሞች በዚህ ሁኔታ እንደሚከበር ያስታወቀው ሠራተኞችን የሚወክለው ተቋም፣ የፀጥታ ችግር አለባቸው ባላቸው ባሕር ዳር እና ኮምቦልቻ ከተሞች ግን ታስቦ እንደሚውል ገልጿል። ባለፈው ዓመት በዓሉን በአደባባይ እንዳያከብር በመንግሥት ተከልክሎ የነበረው ኢሰማኮ፤ በዚህኛው ዓመት ግን ጫና ወይም ክልከላ ተደርጎበት ሳይሆን በራሱ ፈቃድ በአደባባይ ማክበሩን እንደተወው አስታውቋል። ኢሰማኮ የኢትዮጵያ ሠራተኞችን ፈተና ውስጥ ጥለዋል ያላቸው የሰላም መታጣት እና የኑሮ ውድነት ችግሮች መፍትሔ እንዲበጅላቸው መንግሥትን ጠይቋል።

ኢሰማኮ ሀገር አቀፍ የስራ ማቆም እንደሚጠራ አስጠነቀቀ


የሠራተኞች ቀን ለምን ይከበራል?
ለሠራተኞች መብትና ጥቅም መከበር መስዋእት የሆኑ ቀደምት ሠራተኞችን ለማሰብና የሠራተኞችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚከበረው አለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለሠራተኞች ሕልውና ፈተና የሆኑት የሰላም መታጣት እና የኑሮ ውድነት አንገብጋቢ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ እንሰጣቸው በመጠየቅ ነገ በአዳራሽ ውስጥ የሚከበር መሆኑን የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ተናግረዋል። ሠራተኞች የሕይወት፣ የአካል፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳቶች ሰለባነታቸው በፊት በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ በሰፋው ጦርነት ፣ አሁን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ጎልቶ መታየቱን ተናግረዋል። "ሠራተኛ ወጥቶ የሚገባው ፣ ሰርቶ የሚኖረው፣ ሰላም ሲኖር በመሆኑ በተለይም በሀገራችን በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት እና ጦርነት ምክንያት ሠራተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።"

የኤኮኖሚ ዕድገትና የሥራ ዕድል ሁኔታ በኢትዮጵያ


ግጭትና ጦርነት በውይይት እና ድርድር እንዲፈታ መጠየቁ
ኢሰማኮ ግጭቶች በድርድር እና ውይይት እንዲፈቱ ፣ አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሠራተኞችም ችግራቸው እንዲታይ አሳስቧል። "መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉትን ግጭቶችና ጦርነቶች በውይይት መፍትሔ እንዲያገኙ ሆደ ሰፊ በመሆን የአንበሳውን ድርሻ እንዲጫወት፣ ታጣቂ ኃይሎችም ፊታቸውን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት እንዲያዞሩና ዘላቂ ሰላም መፍትሔ እንዲያመጡ" ብለዋል። ሠራተኛው ኑሮ ውድነቱን መቋቋም ስላልቻለ የሥራ ግብር እንዲቀነስለትና ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ተግባራዊ እንዲሆን የጠየቀው ኢሰማኮ፣ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ድረስ በሠራተኞች መብት ዙሪያ ንግግር መደረጉንም ኃላፊው ገልፀዋል። በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ሰዎች እና የወደሙ ድርጅቶችን ዝርዝር በተመለከተ "ጥናት እያደረግን ነው" ያሉት አቶ ካሳሁን ፎሎ በሌሎች አካባቢዎችም ይሄው ችግር መበራከቱን የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን በመጥቀስ አስታውሰዋል።

ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን


"ከወር በፊት ሩቅ ሳንሄድ እዚህ ሙገር አካባቢ ወደ ስልሣ ሠራተኞች ታግተው ከ ሦስት ቀን ነው ከ አራት ቀን በኋላ ነው የተፈቱት። ወንጂ አካባቢ አምስት ሠራተኞች ታግተው በኋላም ተገድለዋል ማለት ነው"

አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW


የደሞዝተኞች ኑሮ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መሆን
በብዙ የሙያ ዘርፎች የተሠማሩ ሠራተኞች በደሞዝ ማነስ ምክንያት ሕይወታቸው እየተፈተነ ነው። ለአብነትም፤ ብዙ ዓመታት በርትተው የተማሩ፣ በየ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ብቃት ያሳዩ ተማሪዎች በተለይ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን የሕክምና ሙያ ዘርፍን እየተቀላቀሉ ቢሠሩም በደሞዝ ማነስ ምክንያት ሲቸገሩ ማድመጥ እየተለመደ ነው። ከሳምንታት በፊት የመኖሪያ ቤት ኪራይን የተመለከተው አዋጅ በሕዝብ እንደራሴው ምክር ቤት ሲፀድቅ፤ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ "አዲስ አበባ ውስጥ ተቀጣሪ ሠራተኞች ከገቢያቸው እስከ 70 በመቶውን፣ አልፎ አልፎም ሙሉ ገቢያቸውን ለቤት ኪራይ እንደሚያውሉ" በመግለጽ በተጨበጭ ደሞዝተኛው ሠራተኛ የገባበትን አጣብቂኝ ገልፀው ነበር።


ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ