1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦታ ይገባኛል ዉዝግብ፤ ከጠ/ሚዉ እንወያይ ጥያቄ፤ የሰብዓዊ ርዳታ ማሰባሰብያ ለኢትዮጵያ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 11 2016

የአማራና የትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት መከሰቱ ለምን? ጠ/ሚ አቢይ አሕመድ ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ጋር እንዲወያዩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት መጠየቁ፤ በኢትዮጵያ ለሚታየዉው የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት በመንግሥትና ዓለምአቀፍ አጋሮች በተጠራው የገንዘብ ማሰባሰብ 610 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡ።

https://p.dw.com/p/4ezP8
ፎቶ ማህደር ፤ የአላማጣ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቦታቸዉ ሲመለሱ
ፎቶ ማህደር ፤ የአላማጣ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቦታቸዉ ሲመለሱምስል Sintayehu Seid/Alamata Youth League

የቦታ ይገባኛል ዉዝግብ፤ ከጠ/ሚዉ እንወያይ ጥያቄ፤ የሰብዓዊ ርዳታ ማሰባሰብያ ለኢትዮጵያ

የአማራ እና የትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞንኛ ዉዝግብ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከጋዜጠኞች ጋር እንዲወያዩ ጥያቄ መቅረቡ፤ እንዲሁም የሰብዓዊ ርዳታ ማሰባሰብያ ለኢትዮጵያ በተሰኙ ርዕሶች ስር የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምቀን ይዘናል።

የአማራ እና የትግራይ ክልል የቦታ ይገባኛል ዉዝግብ

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በቅጡ ባላገገሙት የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ካለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም በአለማጣ ግጭት መከሰቱ ተሰምቷል። ለመሆኑ ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት ገፈት ቀማሽ ለሆኑት እና አሁንም ድረስ በቅጡ ላላገገሙት ለሁለቱ ክልሎች ግጭት መፍትሄ ይሆናል? ሰላማዊ መፍትሄስ ለምን አማራጭ አልሆነም?።

ቲክ ሰመራ ሎጊያ የተባሉ የማህበራዊ ሚዲa ተጠቃሚ ጦርነት መቸም ቢሆን መፍትሄ አይሆንም ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። ጦርነት መቼም መፍትሄ አይሆንም። በሁለቱ ወገን የጦርነቱ ቀስቃሽ አመራሮች አያሌ ወጣት ካገዳደሉ እና አካለ ጎደሎ ካስደረጉ በኋላ፤ መጨረሻ ላይ እነሱ ይጨባበጣሉ። ይሞጓጎሳሉ። ሁሉም መሬቱን እና ግዛት ማስፋፋትን እንጅ ስለ ህዝቡ ህልውና ደንታ የላቸውም፤ ብለዋል። ሲሳይ የማርያም ልጅ የተባሉ ሌላዉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ ሁለቱም ክልሎች የሚጋሩት ልክ እንደ አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ መገንባት፤ እናም የሁለቱንም ክልሎች ተጠቃሚ ማድረግ፤ ሲሉ ምክረሃሳብ ብጤ ጣል አድርገዋል።

ፍጡም መብራቱ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ጦርነት መፍትሄ አይደለም ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። በመጀመሪያ ደረጃ የፈለገ ያህል ልዩነት ቢኖር እንኳን ጦርነት መፍትሄ አይደለም። ከዛ ቀጥሎ ደሞ የፕሪቶሪያ ስምምነት የተካሄደው በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ነዉ። ስለዚህ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ጥሰሃል ብሎ መክሰስ ያለበት ፌደራል መንግስት ነዉ እንጂ የአማራ ክልል መንግስት አይመለከተውም፤ ሲሉ አሳባቸዉን ደምድመዋል።

መርግያ ግደይ በበኩላቸዉ በመጀመርያ ደረጃ ይላሉ፤ በመጀመርያ ደረጃ አማራ እና ትግራይ አልተጋጩም። የተጋጩት የግዜው ሹማምንት እና መከላከያ ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ ይኼ የኔ ነው፤ በማለት ሳይሆን በሕገ-መንግስቱ መግባባት ካልተቻለ፤ ሕገ-መንግስቱ እስኪቀየር ባለው ተስማምተን፤ በቅጣይ ታሪክ በማጣቀስ የትግራይ ታሪካዊ ይዞታዎች አማራ ክልል ውስጥ አሉ የሚባሉ ስላሉ፤ አማራ ክልልም የኔ የሚላቸው ስላሉ፤ በሁለቱም በኩል የሙሁራን መድረክ ተዘጋጅቶ በገለልተኛ መዳኘት የሚሻል ይመስለኛል ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ታሪኩ ኃይሉ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ ያለፈው ጦርነት ብዙ ወገኖቻችንን አሳጥቶናል። የአካል ጉዳት፤ ስደት፤ ረሀብ፤ መፈናቀል በጣም ብዙ ችግሮች አስከትሎ ገና ጠባሣው ሳይሽር ለሌላ ከስከፊ ጦርነት መዘጋጀት፤ በጣም አሳሳቢ እና አስጨናቂ ጉዳይ ነው። ስላማችንን ሳናረጋግጥ፤ ልማታችንን ማረጋገጥ አንችልም።የአማራ እና የትግራይ አመራሮች እንዲሁም የፌዴራል መንግስት በመነጋገር እና ህዝቡን በማወያየት መፍትሄ መስጠት አለበት ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

እዮብ አለማየሁ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። በአሁኑ ወቅት የአማራ ህዝብ ራያ እና ወልቃይትን ይቅርና የራሱ ክልል መሬት በብልጽግና መከላከያ ሰራዊት ተወሮበት ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአማራ ህዝብ የራሱ ነጻነት፤ በብልጽግና መንግስት ተነጥቆበት እና ድምጽ ያሰሙ ፖለቲከኞቹ ታስረው፤ ተገለው እና ተሰደውበት ይገኛል፡፡

የብልጽግና መንግስት፤ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በሚደረግበት እና፤ በሚፈረምበት ግዜ፤ ለቁማር ሲጠቀምባቸው የነበሩትን፤ የኤርትራን እና የአማራ ህዝብን አላካተተም፡፡ ሁለቱም ወገኖች ሂደቱን እና ስምምነቱን የሰሙት ከሚዲያ ነው፡፡ ያሰፈራቸውን የአማራ ታጣቂዎች ከራያ፣ ሲያስወጣ እንዲሁ የአማራ ክልልን ሳያሳውቅ የተፈጸመ ነው፡፡

ሰፊው የአማራ ህዝብ በብልጽግና የሰሞኑ ሴራ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለበት፡፡ የትግራይ ህዝብና መንግስት ከአማራ ህዝብ ጋር ላለመጣላት በትክክለኛ መስመር እና የጥንቃቄ አካሄድ በመሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም የአማራ ህዝብ ከትግግይ ህዝብ ጋር ላለመጋጨት መጠንቀቅ አለበት ሲሉ እዮብ አለማየሁ በቃል አጋኖ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና የጋዜጠኞች ጥያቄ

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉትን ተከታታይ ውይይት ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ጋርም እንዲያካሂዱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠየቀ ይላል በዚህ ሳምንት የተሰማዉ ዜና። ምክር ቤቱ የውይይት ጥያቄውን ከሦስት ሳምንት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ማስገባቱን እና ምላሽም እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ምስል Office of Prime minister of Ethiopia

ስልጣኑ ጥሩወርቅ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ግራ የገባን ጉዳይ እኮ... እውነቱን አፍረጥርጦ የሚጠይቅ ሳይሆን አመስግኖ አጨብጭቦ የሚወጣ የሃይማኖት በለው የባለሐብት... ወይም የሚዲያ ተወካይ ብቻ እኮ ነዉ ያለዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ብሩስ አራርሶ የተባሉ አስተያት ሰች በበኩላቸዉ ጋዜጠኞቹ እኮ ያሉት ከሀገር ውጪ እና እስር ቤት ነዉ። የት ነዉ የሚወያዩት? ሲሉ አስተያየታቸዉን በጥያቄ ደምድመዋል።

ገበየሁ ኤምጊ የተሰኙ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ እንደዉ የሚያነሱላቸዉ ጥያቄ፤ እንደው የተኛሉ የሚተኙበት ጊዜ አሎት የሚል ጥያቄ ነው የሚያነሱላቸዉ ሲሉ ቀደም ሲል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ዉይይት ላይ የተጠየቁትን ጥያቄ አስታዉሰዉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል።

ጥቁር ሰዉ የሚል የፌስቡክ መለያ ያላቸዉ፤ የካድሬን ጥያቄ ያልመለሱ እንዴት ነዉ የጋዘጠኞችን ጠንካራ ጥያቄ ሊመልሱ የሚችሉት ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን ዘግተዋል።

አብዱ ፍቅር የተባሉ አስተያየት ሰጭ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይበርዳቸዉ አይሞቃቸዉ፤ በራሳቸዉ ዓለም የሚኖሩ ንጉሥ እኮ ናቸዉ እሳቸዉ ቤት ጦርነት የለም። ረሐብ የሚባልም አያውቃቸውም ብለዉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ዳንኤል ጊዛይ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ጋዜጠኛ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ እንዴ? ሲሉ ይጠይቃሉ። ጋዜጠኛ አገርቤት የተወሰነው ዘረኝነትና ጥላቻ ያናወዘው ነው። ብዙው ደግሞ ሆድ አደር ነው። በመርህ የሚመራ ጋዜጠኛ ለመሆኑ አለ? አስተያየት ሰጭዉ ሁለተኛ ጥያቄ አስቀምጠዉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ፎቶ ማህደር፤ ታበን ብለዉ ሰልፍ የወጡ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል
ፎቶ ማህደር፤ ታበን ብለዉ ሰልፍ የወጡ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ምስል Alemenw Mekonnen/DW

የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የሰብዓዊ እርዳታ ማሰባሰብያ

በኢትዮጵያ ላለው የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ምላሽለመስጠት በኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች በተጠራው የገንዘብ ማሰባሰብ ሥነ ሥርዓት 610 ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበ። ጄኔቫ ስዊዘርላንድ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ለ 15.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሕይወት አድን ድጋፍ ለማድረግ 3.24 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ ከ 21 ለጋሾች ማሰባሰብ የተቻለው 610 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

ህይወት ወልዳይ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ መንግስት የለንም እሁን ያለው ንጉስ ንግስናውን ብቻ ለሚጠብቁለት እና ለንጉሱ ቤተመንግስት ብቻ ይገነባል እንጂ ስለ ተራቡት እይመለክተውም !

ጋሽ ዘሪሁን የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ ለጦርነት ይሆናል መቼም። እዚህ አገር ልማት ወንጀል ነው የተባለ ይመስላል። ራስ በራሳችን መባላት ተይዘዋልሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

አልያን አልያን የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ እዉነት ለችግረኞች እረሃባቸዉን ማስታገሻ ከሆነ ጥሩ ነዉ ግን አይመስልም ድሮን መግዣ፣ቤተ-መንግሥት መገንቢያ የሚዉል ይመስላል። የሆኖ ሆኖ ለጋሾችን እናመሰግናለን ሲሉ አልያን አልያን አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ