1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሙስና

የቀሲስ በላይ መኮንን የችሎት ውሎ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 24 2016

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ዛሬ በዋለው ችሎት ቀሲስ በላይ መኮንን በተጠረጠሩበት «ከባድ የሙስና ወንጀል» ላይ ክስ ለመመስረት ዐቃቤ ሕግ የጠየቀውን የ 15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቀደ ። ዐቃቤ ሕግ፦ ድርጊቱ «ከባድ የሙስና ወንጀል» እና ከዐሥር ዓመት በላይ የሚያስጠይቅ መሆኑን ለችሎቱ አስረድቷል ።

https://p.dw.com/p/4fQzb
Äthiopien | Bundesgericht in Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

ቀሲስ በላይ መኮንን ላይ 15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ዛሬ በዋለው ችሎት ቀሲስ በላይ መኮንን በተጠረጠሩበት «ከባድ የሙስና ወንጀል» ላይ ክስ ለመመስረት ዐቃቤ ሕግ የጠየቀውን የ 15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቀደ ። ዐቃቤ ሕግ ቀሲስ በላይ መኮንን እና «ግብረ አበሮች» የተባሉ ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች አፍሪቃ ኅብረት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ሊፈጽሙት ነበር ያለው «ከባድ የሙስና ወንጀል» ከዐሥር ዓመት በላይ የሚያስጠይቅ መሆኑን ለችሎቱ አስረድቷል ።

በችሎቱ የተገኙ ስድስት የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኛቸው የተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብት የሚያስከለክል አለመሆኑን በመጥቀስ በዋስትና እንዲወጡ፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ ተጠርጣሪዎችም ያለ አግባብ መያዛቸውንና የተጠየቀው የክስ መመስረቻ ጊዜም ተገቢ አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ ቀሲስ በላይ መኮንን የተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብት የሚያሰጥ አለመሆኑን በመግለጽ የክስ መመስረቻውን 15 ቀን ፈቅዶ በሚገኙበት ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትእዛዝ ሰጥቷል ።

የዛሬው የችሎት ውሎ ዝርዝር ጉዳዮች

ሊቀ ዐዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ከሁለት ሳምንት በፊት የአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብ "ከኅብረቱ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ" በተባሉ ሀሰተኛ ሰነዶች በመጠቀም ከአፍሪቃ ኅብረት የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ ሒሳብ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማዘዋወር ሲሞክሩ ተገኝተዋል በሚል በፖሊስ ተይዘዋል።

ምስክር ተሰምቶ የፍሬ ነገር ክርክር የማይደረግበት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መርማሪዎች በተሰጠው ተጨማር የምርመራ ጊዜ ምን አከናወኑ የሚለውን ለማድመጥ ነበር ዛሬ የተሰየመው።

ዐቃቤ ሕግ ለሦስተኛ ጊዜ የቀረቡት ቀሲስ በላይ መኮንን የተጠረጠሩበት ወንጀል "ከባድ የሙስና ወንጀል" በመሆኑ እና ይህ የወንጀል ድርጊት ከ አሥር ዓመት በላይ የሚያስጠይቅ በመሆኑ እና የፖሊስ የምርመራ መዝገብ የደረሰው ዛሬ መሆኑን በመጥቀስ "የክስ መመስረቻ" 15 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ዐቃቤ ሕግ ገና ክስ አለመመስረቱን መግለጹ ተገቢ እንዳልሆነ፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል ውስብስብ እንዳልሆነ፣ የተጠየቀው 15 ቀን የክስ መመስረቻ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰው ተከራክረዋል።

ቀሲስ በላይ መኮንን
ቀሲስ በላይ መኮንንምስል Privat

ከተጠርጣሪዎች "ማን ምን አደረገ" የሚለውን የሚያሳይ መረጃ አለመቅረቡን የገለፁት ጠበቆች "የምርመራ መዝገቡ ተዘግቶ ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና እንዲለቀቁ" በሚል ተጠርጣሪዎቹ በመጥሪያ ቀርበው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ፣ ጽኑ የዋስትና መብትን የሚጥስ ወንጀል አለመፈፀማቸውንም ጠቅሰው ተከራክረዋል። ከተከሳሽ ጠበቆች አንደኛውን ጠበቃና የሕግ አማካሪ ብርሃኑ በጋሻውን ጠይቀናቸዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ "ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር" እንደሚሠራ ለችሎቱ አስረድቷል። አክሎም ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት የሚያስከለክል ድርጊት መፈፀማቸውን የጠቀሰበት የሕግ አንቀጽ "ሕጋዊ፣ ሥነ ሥርዓታዊ እና ምክንያታዊ" መሆኑንም ጠቅሶ ተከራክሯል።

የማታለል ድርጊት ሊፈፀምበት የነበረው የመንግሥት የልማት ድርጅት ከሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር ያለው ዐቃቤ ሕግ ፣ ይህም የዋስትና መብትን የሚከለክል በመሆኑ ጠበቆች ያነሱት መከራከሪያ ውድቅ እንዲደረግለት ችሎቱን ጠይቋል።

ሁለተኛ እና ሦስተኛ ተጠርጣሪዎችም የድርጊቱ "ግብረ አበሮች" በመሆናቸው እንደ ዋና ወንጀል አድራጊ ይታያሉ ሲልም ተከራክሯል። ጠበቃና የሕግ አማካሪ ብርሃኑ በጋሻው የቀጣይ ሂደት ምን ሊሆን እንደሚችልም ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

የአፍሪቃ ኅብረት በአዲስ አበባ ከተማ
የአፍሪቃ ኅብረት በአዲስ አበባ ከተማምስል Solomon Muchie/DW

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ ቀሲስ በላይ መኮንንየተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብት የሚያሰጥ አለመሆኑን በመግለጽ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የክስ መመስረቻ 15 ቀን ፈቅዶ በሚገኙበት ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ይህ ድርጊት የተፈፀመበት የአፍሪካ ሕብረት በቅጥር ግቢው ውስጥ ባለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳቦቹ 6 ሚሊዮን ዶላር ለማጭበርበር የተደረገበትን ሙከራ ማክሸፉን ትናንት አስታውቋል። ተቋሙ "የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዘዋውር ነው" በሚል ስለተሰራጨው መረጃ ግን ያለው ነገር የለም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ይህ የተሰራጨው መረጃ "የተሳሳተ" መሆኑን ከሕብረቱ ጋር ባደረገው ቀጥተኛ ውይይት መረዳቱን ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ