1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የብሪታንያ ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ውሳኔ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2016

ከሀገር ውስጥ ተቃውሞም ድጋፍም የሚሰነዘርበት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላክ የሚያስችለው የብሪታንያ ሕግ ከዓለም አቀፍ የመብት ተከራካሪ እንዲሁም የስደተኞች መርጃ ድርጅቶች ብርቱ ተቃውሞ ተሰንዝሮበታል። የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የብሪታንያ ቅርንጫፍ ሃላፊ ሳሻ ዴሽሙክ ሕጉ ሁለት ስህተቶች አሉት ይላሉ ።

https://p.dw.com/p/4fN97
UK, London | Ruanda Abstimmung im Unterhaus
ምስል House of Commons/UK Parliament/PA Wire/empics/picture alliance

አወዛጋቢው የብሪታንያ ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ውሳኔ

ብሪታንያ ሕገ-ወጥ የምትላቸውን ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ማባረር የሚያስችላትን አወዛጋቢ ሕግ ካጸደቀች ዛሬ አንድ ሳምንት ሆነ። በትናንሽ ጀልባዎች በእንግሊዝ ቻናል በኩል ብሪታንያ የገቡ ተገን ጠያቂዎችን የሚመለከተው ይኽው ሕግ በዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾችና የስደተኞች ጉዳይ በሚመለከታቸው ድርጅቶች ክፉኛ ተተችቷል።
የብሪታንያ የሕግ ወወሰኛ ምክር ቤት የዛሬ ሳምንት ያጸደቀው ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ መላክ የሚያስችለው ሕግ፣ ሕግ ሆኖ ለመውጣት ባጋጠመው ፖለቲካዊና ሕጋዊ ፈተናዎች ምክንያት ከሁለት ዓመት በላይ ወስዶበታል። ሀሳቡ የቀረበው በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓ.ም. ሲሆን ዓላማውም ከሰሜን ፈረንሳይ በትናንሽ ጀልባዎች በእንግሊዝ ቻናል በኩል ወደ ብሪታንያ የሚካሄድ ሕገ ወጥ የሚባለውን ፍልሰት መቀነስ ነበር። ይህን ለማሳካትም በሚያዚያ 2022 ዓም የያኔው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን መንግሥታቸው ሕገ ወጥ የሚባሉ ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ እንደሚያባርር አሳወቁ።የብሪታኒያ ተገን ጠያቂዎችን ወደ ርዋንዳ ለማጓጓዝ የያዘችው ዕቅድ


«ከዛሬ ጀምሮ የኛ አዲሱ የፍልሰትና የኤኮኖሚ ልማት አጋርነት ማለት፣ ማንም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ብሪታንያ የሚገባ እንዲሁም ከጎርጎሮሳዊው ጥር አንድ 2022 ዓም አንስቶ በሕገ ወጥ መንገድ ብሪታንያ የገቡ አሁን ምናልባት ወደ ሩዋንዳ ይወሰዳሉ። ይህ እንደ አዲስ ግኝት የሚቆጠር አሰራር የመነጨው ከጋራ ሰብዓዊ አስተሳሰባችን ነው። ስራ ላይ መዋል የሚችለው ደግሞ ብሬክዚት በሰጠን ነጻነቶች ነው። አዲሱ አሰራር ለተገን ጠያቂዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ ሕጋዊ መንገዶችን የሚከፍት የሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎችን ገንዘብ ማግኛ መንገድ የሚዘጋ ነው።

የቀድሞ የብሪታንያ ቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን
የቀድሞ የብሪታንያ ቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ምስል Matt Dunham/AP Photo/picture alliance


በዚያው ዓመት መንግስት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ቢዘጋጅም በወቅቱ የአውሮጳ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ምክንያት ተገን ጠያቂዎቹ ከተሳፈሩበት አውሮፕላን እንዲወርዱ ተደርጓል። የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሩዋንዳ ደኅንነቷ የተጠበቀ አገር አይደለችም በሚል ሕጉን በተደገጋሚ ተቃውሞ ውሳኔዎችን አሳልፎም ነበር። ይሁንና መንግሥት ከሕግ አንጻር ለሚነሱበት ጥያቂዎች መልስ ይሰጣሉ ያላቸውን ማሻሻያዎች በማድረግና ከሩዋንዳ ጋርም ሌላ ስምምነት በመፈራረም ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ የሚያስችለው ሕግ በሀገሪቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ጸድቋል። ለበርካታ ዓመታት ብሪታንያ የኖረው አንጋፋው የለንደኑ ዘጋቢያችን ድልነሳ ጌታነህ ፍርድ ቤቶች አልተሟሉም ሲሉ ያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎችንና መንግሥትም ያደረጋቸውን ማሻሻያዎች እንዲሁም ከሕጉ ጋር የተያያዙ ስጋቶቹን ያካፍለናል።

ባለፉት አራት ወራት ብቻ 6265 ተገን ጠያቂዎች በሰሜን ፈረንሳይ አድርገው በእንግሊዝ ቻናል በኩል በትናንሽ ጀልባዎች ብሪታንያ የባህር ዳርቻ ደርሰዋል። ከዛሬ 6 ዓመት ወዲህ በአጠቃላይ 120,500 ተገን ጠያቂዎች ብሪታንያ ገብተዋል። መንግሥት ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ መወሰኑ ከሀገር ውስጥ ብዙ ተቃውሞ አስነስቶበታል። ከመካከላቸው አንዱ እኚህ የ73 ዓመት አዛውንት ይገኙበታል። የመንግሥትን ውሳኔ እብደት ብለውታል።«እንደሚመስለኝ ፍጹም ትርጉም የለሽ ነው። ወደፊት ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው የሚሆነው። ተገን ጠያቂዎቹ የሚላኩባቸው ሀገራት በምንም መንገድ ደኅንነታቸው የተጠበቀ አይደለም። በሩዋንዳ ከጥቂት ዓመታት በፊት የዘር ማጥፋት ወንጀል ነበር። እንደሚመስለኝ ይህ ፍጽም እብደት ነው።»
አዛውንቱ ማይክ አላናና ሌሎች ይህን ሲሉ ሕጉን የሚደግፉም አልጠፉም። እኚህ የ68 ዓመት ጡረተኛ ደግሞ መባረር አለባቸው ይላሉ።
« የኛ ሃላፊነት ስላይደለ መላክ አለባቸው። ሃላፊነታችን የኛን ሰዎች መንከባከብ ነው፤ይህን ግን አናደርግም ።»

ስደተኞች በትንሽ ጀልባ በእንግሊዝ ቻናል ላይ
ስደተኞች በትንሽ ጀልባ በእንግሊዝ ቻናል ላይምስል Dan Kitwood/Getty Images


ከሀገር ውስጥ ተቃውሞም ድጋፍም የሚሰነዘርበት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላክ የሚያስችለው የብሪታንያ ሕግ ከዓለም አቀፍ የመብት ተከራካሪ እንዲሁም የስደተኞች መርጃ ድርጅቶች ብርቱ ተቃውሞ ተሰንዝሮበታል። የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የብሪታንያ ቅርንጫፍ ሃላፊ ሳሻ ዴሽሙክ ሕጉ ሁለት ስህተቶች አሉት ይላሉ
«የሩዋንዳው ደንብ ስህተት የሚሆነው ስለስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች መብት በዓለም አቀፍ ሕግ የተደነገገውን መጣሱ ብቻ አይደለም ስህተት የሚሆንበት ሁለተኛ ምክንያትም አለ ።ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ለመስጠት መረጃዎችን በተገቢው መንገድ እንዳይመረምሩና እንዳያጠኑ መጥፎ የሚያስገድድ ሕግ መንግሥት ላወጣ እችላለሁ ብሎ መዛቱ ነው ።ይህ በጣም አሳሳቢ ና መጥፎ አብነት የሚያስከትል ነው። ይህ ማለት ለስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መርኅ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ሊንጸባርቅ የሚችል ነው። »

ጀርመን ተቀባይነት ያላገኙ ተገን ጠያቂዎችን ለማስወጣት ሕግ አፀደቀች
የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቢሮ ሃላፊዎች የብሪታንያን ሕግ በዓለም አቀፉ ደረጃ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር እና ለስደተኞች ጥበቃ የማድረግ ሃላፊነቶችን መጋራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖዎች የሚያሳድር ሲሉ ተቃውመውታል። የየሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቢሮ ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ ሕጉን በብሪታንያ የሕግ የበላይነትን ወደ ኋላ የሚጎትት እና በሌላው የዓለም ክፍል ላይም አደገኛ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያስቀምጥ ሲሉ ተችተውታል። «በብሪታንያና ሩዋንዳ የተገን አሰጣጥ አጋርነት ብሪታንያ የሚገኙ ተገን ጠያቂዎች የተገን ማመልከቻቸው ብሪታንያ ውስጥ መደመጥ ከመቻሉ በፊት ወደ ሩዋንዳ ይወሰዳሉ። ይህ ደግሞ እኛ እንደምናስበው ከዓለም አቀፉ ትብብርንና ሃላፊነት መጋራት ጋር የሚጣጣም አይደለም። ከዚህ በተጨማሪም ብሪታንያ ራሷ ከፈራሚዎቹ አንዷ የሆነችውን የ1951 ዱን የስደተኞች ስምምነት ይጥሳል። »ለተገን ጠያቂዎቹ ከፈረንሳይ ወደ ብሪታንያ መሻገሪያ በሆነችው ካሌ የሚገኘው ቻሪቲ ኬር የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ባለአደራ፣ ጠበቃ ጀምስ ኒኮል ውሳኔውን የተገን ጠያቂዎቹን ችግር የሚያባብስ ሲሉ ነቅፈውታል።

የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክምስል Toby Melville/AP Photo/picture alliance


«ውሳኔው ለስደተኞች በጣም ጎጂ ነው። ጨካኝ ፖሊሲ ነው። ስደተኞች አሉን፤ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ይህ ማስታወቂያ የደረሳቸውን ስደተኞችን አነጋግረናል። በግዳጅ ከሀገሪቱ እንደሚባረሩ እንደተነገራቸው ነግረውናል። እነዚህ ጦርነት ከሚካሄድባቸው ሀገራት የመጡ ናቸው። የስነ ልቦና ስብራት ደርሶባቸዋል ስሜታቸውም የተጎዳ ስዎች ናቸው።ይህ በስቃያቸው ላይ የሚደመርና ተጨማሪ ጭንቀት የሚያስከትልባቸው ነው። ይህ ፍጹም ቅሌት ነው።» የብሪታንያ የብሔራዊ የኦዲት ቢሮ ከዚህ ቀደም እንዳስታወቀው ተገንን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመውሰድ በመቶ ሚሊዮኖች ፓውንድ የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልጋል። የመጀመሪያዎቹን 300 ተገን ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ለማጋዝ ብቻ በእያንዳንዱ ሰው ወደ ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ ወጪ ያስፈልጋል ነው ያለው ቢሮው። በዚያ ላይ ደግሞ ድልነሳ እንደሚያስረዳውብሪታንያ ከሌሎች የአውሮጳ ሀገራት ጋር ሲነፃጸር አነስተኛ የሚባል ቁጥር ያላቸው ተገን ጠያቂዎች የሚገኙባት ሀገር ሆና ይህን ያህል ገንዘብ አውጥታ ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ መዘጋጀቷ አስገርሟል ። የአውሮጳ ኅብረት የፍልሰትና የጥገኝነት አሳጣጥ ፖሊሲ ማሻሻያ

የብሪታንያ መንግሥት የተገን አሰጣጥ ስርዓት በኛ ፍላጎት እንጂ ለሰዎች አሻጋሪ ደላሎች ገንዘብ በመክፈል አቅም አይወሰንም ሲል ይከራከራል።
ያም ተባለ ይህ ሕጉ እንደጸደቀ ከአሁን ወዲያ ተገን ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ከመላክ የሚያግደን አይኖርም ሲሉ የተናገሩት የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ስደተኞቹን ወደ ሩዋንዳ የመላኩ ስራ በአስር እና 12 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ