1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰሞነኛው «የትራንስፖርት እቀባ» እና ተጽእኖው

ዓርብ፣ ሚያዝያ 11 2016

ባለፈው ሳምንት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር በተገደሉበት ምሥራቅ ሸዋ ዞን መቂ ከተማ ከሰሞኑ በኅቡዕ ታወጀ ከተባለው የመጓጓዣ አገልግሎት እቀባ ጋር በተያያዘ ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱ እየተነገረ ነው።

https://p.dw.com/p/4ezTe
Äthiopien I Keine Bewegung in der Region Oromia - Militante hatten vor jeder Bewegung gewarnt
ኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያምስል Seyoum Getu/DW

የእቅስቃሴ ገደብ በኦሮሚያ

ባለፈው ሳምንት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር በተገደሉበት ምሥራቅ ሸዋ ዞን መቂ ከተማ ከሰሞኑ በኅቡዕ ታወጀ ከተባለው የመጓጓዣ አገልግሎት እቀባ ጋር በተያያዘ ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱ እየተነገረ ነው። ባለፈው ሰኞ ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሌሊቱ 8፡00 በከተማዋ 01 ወይም ኦዳ ቀበሌ በሚባለው አካባቢ የተወሰኑ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን የዐይን እማኞች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ተጠርቷል የተባለው የመጓጓዣ እቀባ ማኅበረሰቡን ለችግር መዳረጉም ነው የተገለጸው።

የፖለቲከኛውን «አሰቃቂ ግድያ» ተከትሎ በኅቡዕ ተጠርቶ ለማኅበረሰቡ ተሰራጭቷል በተባለው በሰሞነኛው የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት እቀባ በርካታ ቦታዎች ላይ መደበኛ ፍሰቱ ስለመቀጠሉ ቢነገርም በተወሰኑት ቦታዎች ላይ መስተጓጎል ስለማጋጠሙ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

የተሽከርካሪዎች ቃጠሎ

ፖለቲከኛው በተገደሉበት መቂ ከተማ ደግሞ ባለፈው ሰኞ ከእኩለ ሌሊት በኋላ በከተማዋ ቆመው የነበሩ ተሸከርካሪዎች ማንነታቸው ባልታወቀ አካላት መቃጠላቸውን አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ስሜ ይቆይ ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ «አንድ ፒካፕ ተሽከርካሪ፣ አንድ ተሳቢ ቦቴ እና ሁለት-ሦስት ባጃጅ የተባሉ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል። ክስተቱ ሰኞ ሌሊት 8፡00 ገደማ ነው የተደረገው። ቦታው 01 ቀበሌ ወይም ገንዳ ኦዳ ይባላል። ተሽከርካሪዎቹ በቆሙበት ነው የተቃጠሉት» ብለዋል።

ሌላው አስተያየት የሰጡን የአካባቢው ነዋሪ በፖለቲከኛው ግድያ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ብስጭት መፈጠሩን በማስረዳት የመጓጓዣ እቀባውም ከሰሞኑ ታውጆ ፍሰቱም በእጅጉ መቀነሱን ገልጸዋል። እኚህ አስተያየት ሰጪ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴበዚህ አካባቢ ከወትሮው ከግማሽ በላይ የቀነሰ ነው ሲሉም ትዝብታቸውን አጋርተውናል። «ተሽከርካሪዎች እምብዛም አይንቀሳቀሱም። መጀመሪያ ለአምስት ቀን በሚል ነበር የእንቅስቃሴ ገደቡ የተጠራው። ግን ዛሬም አምስተኛውን ቀን አልፎ ብዙም እንቅስቃሴ አይስተዋልም» ነው ያሉት።

በአካባቢው ተፈጸመ ስለተባለው የተሽከርካሪዎች ቃጠሎ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠው በመንገዱ ግን አሁንም ድረስ ተሽከርካሪዎች እንደሚንቀሳቀሱበት ያስረዱት የመቂ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኮማንደር መሀመድ ሱፋ፤ ስብሳባ ላይ መሆናቸውን አስረድተው ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የእርሻ ስፍራ በኦሮሚያ ክልል
ፖለቲከኛው አቶ በቴ ዑርጌሳ በተገደሉበት መቂ ከተማ ደግሞ ባለፈው ሰኞ ከእኩለ ሌሊት በኋላ በከተማዋ ቆመው የነበሩ ተሸከርካሪዎች ማንነታቸው ባልታወቀ አካላት መቃጠላቸውን አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።ፎቶ ከማኅደር፤ የእርሻ ስፍራ በኦሮሚያ ክልል ምስል Seyoum Getu/DW

የትራንስፖርት ፍሰት ገደብ ተጽእኖ

ሰሞነኛው በኦሮሚያ በኅቡዕ ተጠራ የተባለው የትራንስፖርት ማዕቀቡ ተግባራዊ በሆነባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠሩን ነዋሪዎች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። አንድ የምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ ነዋሪ፤ «ከእሑድ ጀምሮ ጊዳ - ነቀምት አቅጣጫ እገዳ በመኖሩ ተሸከርካሪዎች አይሄዱም። ከዚህ ወደ እኛ ወደ ኪረሙ ግን የሚመጡ ነበሩ። አሽከርካሪዎች ተላለፈ የተባለውን ጥሪ ፈርተው ነው ያቆሙት» ብለዋል። ይህም ነዋሪው ላይ የፈጠረው ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑንም አስረድተዋል።

ከወሊሶ ወደ አዲስ አበባ ትናንት የተጓዙ መንገደኛ በበኩላቸው እስከ ቀኑ 10 ሰኣት በተለይ ወደ ጅማ መደበኛ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ ቢታይም ከመንገድ የሚገኙ ከተሞች ላይ ግን የእንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ማስተዋላቸውን አንስተዋል።

የመጓጓዣ እንቅስቃሴ መገደቡ በሌሎችም አካባቢዎች ተጽእኖው መታየቱን ከሰሞኑ መዘገባችንም ይታወሳል። ስለተባለው የመጓጓዣ መስተጓጎል ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ብንደውልም ስልካቸውን ባለመመለሳቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ