1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የሱዳን ቀዉስና ዲፕሎማሲዉ

ሰኞ፣ ጥር 13 2016

ዓለም አቀፍ ሕግጋትና ደንቦችን ያረቀቁና ያስፀደቁት ኃያላን ያላከበሩትን ሕግ የካርቱም ጄኔራሎች ያከብራሉ ብሎ ለማሰብ ግን እንደ ሞዲ የዋሕነትን ይጠይቃል።ኢንተቤ-ዩጋንዳ ላይ የተሰየመዉ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሪዎች ጉባኤ ዋና አላማ አዘጋጆቹ-እንዳሉት አሳዛኙ ጦርነት በድርድር እንዲፈታ ለመጠየቅ ነበር።

https://p.dw.com/p/4bYsd
ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዳዶቹ ከአንድ ጊዜ በላይ ለመፈናቀል ተገድደዋል
10 ወራት ያስቆጠረዉ የሱዳን የርስበርስ ጦርነት ከ7ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አፈናቅሏል ወይም አሰድዷልምስል Marie-Helena Laurent/WFP/AP/picture alliance

ማሕደረ ዜና፣ የሱዳን ቀዉስና ዲፕሎማሲዉ

የሱዳንን የርስ በርስ ጦርነት፤ ብዙዎች የሁለት የቀድሞ ወዳጅ ጄኔራሎች ጠብ መዘዝ ይሉታል።አንዳዶች የካርቱም-ልሒቃንና የዳርፉር ገጠሬ ታጣቂዎች ዉጊያ ያደርጉታል።የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን(ኢጋድ) አባል ሐገራትመሪዎች ደግሞ ባለፈዉ ሳምንት «ኢፍትሐዊ» አሉት።ማንም ምን አለዉ ምን ጦርነቱ ባለፉት 10 ወራት ዉስጥ የተለያዩ ድርጅቶች እንዳስታወቁት በትንሽ ግምት ከ12 ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሱዳናዊ ገድሏል።ከ30 ሺሕ በላይ አቁስሏ።ከ7ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አንድም አፈናቅሏል አለያም አሰድዷል።ያን ደግ፣የዋሕ፣ ደሐ ሕዝብ የሚገድል-የሚያሰድድ-የሚያፈናቅለዉ ጦርነት ዛሬም ዳርፉርን፣ ጀዚራን፣ካርቱምን እያወደመ ነዉ።ማብቂያ አለዉ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ሶስቱ ጦርነቶችና የዓለም ሕግ

የዓለም ኃያል፣ሐብታም ሐገራት መንግስታት፣ ኩባንያና ድርቶች መሪዎች ወይም ተወካዮች ለጠንካራ ተፅዕኖ፣ሐብት፣ምቹ ኑሯቸዉ መቀጠል ዳቮስ-ሲዊዘርላንድስ ዉስጥ ሲመክሩ አፍሪቃዊቱ ዩጋንዳ በዲፕሎማሲዉ አገላለፅ አዳጊ የሚባሉትን የድሐ ሐገራት መሪዎችና ባለስልጣናትን ታስተናግድ ነበር።ካምፓላና ኢንተቤን ያጨናነቁት የገለልተኛ ሐገራት ንቅናቄ-ጉባኤ፣ የቡድን 77 ጉባኤ፣የኢጋድ ጉባኤ ተካፋዮች እንደየ ጉባኤዎቹ አላማና ግብ ድሕነትን ከመዋጋት ሰላም እስከማስፈን፣ ከአየር ንብረት፣ እስከ ንግድ ልዉዉጥ በርካታ ርዕሶችን አንስተዉ መክረዋል።የሶስቱም ጉባኤዎች የጋራ ርዕስ የነበሩት ግን ሶስት ጦርነቶች ነበሩ።

በሁለቱ ጉባኤዎች ላይ የተካፈሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እንዳሉት ሱዳን፣ ዩክሬንና ጋዛን የሚያወድሙት ጦርነቶች ሕይወት፣አካል፣ ሐብት ንብረት ብቻ ሳይሆን የዓለም የጋራ ሕግና ደንቦችንም እያጠፉ ነዉ።


«ሰብአዊ መብቶች፣ዓለም አቀፍ ሕጎች፣የጄኔቫ ስምምነቶች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ ያለምንም ምክንያት እየተጣሉ ነዉ።ግጭቶች፣ ከሱዳን እስከ ዩክሬ፣ እስከ ጋዛ እየተቀጣጠሉና እየተጠናከሩ ነዉ።»

የዓለምን ሕግ፣ ስምምነትና ደንቦችን የጣሰዉ ወገን ማንነት ለዓለም ትልቅ ዲፕሎማት አይደለም ለተራዉ ሰዉም የተሰወረ አይደለም።የዓለም ፖለቲካ-ኢኮኖሚ አድራጊ ፈጣሪዎች በቀጥታ ከተመሰጉባቸዉ ከጋዛዉ ዉድመት ቀድሞ፣ ከዩክሬኑ ዉጊያ ተከትሎ ዓምና ሚያዚያ ሱዳን ላይ የተቀጣጠለዉ ዉጊያ ለአፍሪቃ በጣሙን ለምሥራቅ አፍሪቃ የአምና ትልቁ ጦርነት ነዉ።
ጦርነቱ በቀጥታ ከሚፈጀዉ ወይም ከሚያፈናቅለዉ ሕዝብ በተጨማሪ በምግብ እጦትና ኮሌራን በመሳሰሉ በሽታዎች መቶዎችን እየገደለ፣ ሚሊዮኖችን እያሰቃየ ነዉ።አሚና የተባሉ ተፈናቃይ እንዳሉት ለሱዳኖች ካንዴ በላይ መፈናቀል፣ በረሐብና በሽታ መሰቃየት እየተለመደ ነዉ።

ካርቱም ዉስጥ ባለፈዉ ሚያዚያ የተጀመረዉ ዉጊያ ወደሌሎች ግዛቶችም ተስፋፍቷል
ምንቀረ? በጦርነቱ ክፉኛ ከወደሙት የርዕሠ-ከተማ ካርቱም አካባቢዎች አንዱምስል AFP

«ከዳርፉር ወደ ካርቱም ሸሽቼ ነበር።ከካርቱም ደግሞ ወደ ማዳኒ ሸሸሁ እዚያም ዉጊያ ሆነ።እና ፖርት ሱዳን ገባሁ።ለወራት ምግብ፤መድሐኒትም ሆነ መጠለያ አላገኘንም።በጣም መጥፎ ነዉ።»
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ርዳታ ሰጪ ተቋማት እንደሚሉት ዉጊያዉ ሰሜን፣ ምዕራብና ማዕከላዊ ሱዳንን በማዳረሱ በየአካባቢዉ የሰፈሩ ተፈናቃይና በዉጊያ የተቃረጡ ሰላማዊ ሰዎችን መርዳት አልቻሉም።ከዉጊያዉ በተጨማሪ ተፋላሚ ኃይላት ወይም ታጣቂዎች የርዳታ ቁሳቁሶችን ስለሚዘርፉና ሰራተኞችን ስለሚተናኮሉ ለርዳታ ሰራተኞች ከባድ ፈተና ነዉ።
የሱዳን ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች መድረክ የተሰኘዉ ስብስብ አስተባባሪ ኢብራሒም ሞዲ እንደሚሉት ለተቸገረዉ ሕዝብ ርዳታ እንዲደርስ ተፋላሚ ኃይላት ካልፈቀዱ ሁኔታዉ አሳሳቢ ነዉ።
«የርዳታ ሰራተኞች በዚሕ አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ መስራት አይችሉም።ተፋላሚ ኃይላት ዓለም አቀፍ ሕግን ጠብቀዉ ለሚሊዮኖች ርዳታ እንዲደርስ ቅድሚያ መስጠት አለባቸዉ።በጣም አሳዛኝ ነዉ።»
ለብዙዎች ሞዲ እንዳሉት አሳዛኝ ነዉ።ዓለም አቀፍ ሕግጋትና ደንቦችን ያረቀቁና ያስፀደቁት ኃያላን ያላከበሩትን ሕግ የካርቱም ጄኔራሎች ያከብራሉ ብሎ ለማሰብ ግን እንደ ሞዲ የዋሕነትን ይጠይቃል።ባለፈዉ ሐሙስ ኢንተቤ-ዩጋንዳ ላይ የተሰየመዉ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሪዎች ልዩ ጉባኤ ዋና አላማ አዘጋጆቹ-እንዳሉት አሳዛኙ ጦርነት በድርድር እንዲፈታ ለመጠየቅ ነበር።

የኢጋድ ጉባኤ ጥሪና ምክር

ከስምቱ የኢጋድ አባል ሐገራት የጅቡቲ፣ የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳን፣የዩጋንዳ፣ የየሶማሊያ መሪዎች የተካፈሉበት ጉባኤ ባወጣዉ የአቋም መግለጫ «ኢፍትሐዊ» ያለዉን ጦርነት ለማቆም የተፋላሚ ኃይላት ተወካዮች ፊትለፊት ተገናኝተዉ እንዲነጋገሩ አሳስቧል።የኢጋድን ተዘዋዋሪ የሊቀመንበርነት ስልጣን የያዘችዉ የጅቡቲ ዉጪ ጉዳይና የዓለም ዓለም አቀፍ ትብብር ሚንስትር መሐመድ ዩሱፍ ያነበቡት መግለጫ እንደሚለዉ የሱዳኑ ጦርነት ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ ኢጋድ የሚችለዉን ሁሉ ያደርጋል።

«ተፋላሚ ወገኖች ፊትለፊት ተገናኝተዉ የሚነጋገሩ መሆናቸዉን በ14 ቀናት ዉስጥ እንዲያሳዉቁና በሁለት ሳምንት ዉስጥ እንዲገናኙ እንጠይቃለን።የሱዳኑ ጦርነት በሰላማዊ ድርድር እንዲፈታ አባል ሐገራት ያላቸዉን አቅምና ብልሐት በሙሉ እንደሚጠቀሙ አፅንኦት በመስጠት፣የኢጋድ ቢሮ ጉዳዩ የደረሰበትን ደረጃ በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ እንዲያሳዉቅ (ጉባኤዉ) መመሪያ ሰጥቷል።»
የጅቡቲዉ ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌድ የመሩትን ጉባኤ ያስተናገዱት የዩጋንዳዉ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኔ ጉባኤዉ ካሳለፈዉ ዉሳኔ እኩል ለጦርቱ የሰጠዉ ብያኔ ልዩ ትኩረት ያሻዋል አይነት ባይናቸዉ።እንደ አማፂ ቡድን መሪ 6 ዓመት ያዋጉት፣እንደ ፕሬዝደንት ዩጋንዳን 38 ዓመታት የመሩት ሙሴቬኒ እንደ ሐገራቸዉ ሽማግሌዎች ነገርን ቀለል፣ዘርዘር፣ ለስለስ ባሉ ቃላትና ድምፀት ማስረዳት ይወዳሉ።

የ8ቱ የኢጋድ አባል ሐገራት ባንዲራዎች
የኢጋድ አባል ሐገራት ባንዲራዎች-ከእንግዲሕ ሱዳን ትቀነሳለችምስል Yohannes G/Eziabhare

«የሱዳኑን ጦርነት፣ የአቋም መግለጫችንን አይታችሁት ከሆነ፣ ኢፍትሐዊ በማለት ነዉ የገለፅነዉ።እኛ የነፃነት ተዋጊዎች ለነዚሕ ቃላት ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣቸዋለን።ለነፃነት በምንዋጋበት ወቅት የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ጦርነቶቻችን ፍትሐዊ ነበሩ።ምክንያቱም የተዋጋነዉ በሌላ በየትኛዉም መንገድ ልናገኝ ለማንችለዉ ለፍትሕ ነበር።»
መግለጫና ምክሩ በጉባኤዉ ላይ ለተካፈሉት ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ ለጄኔራል መሐመድ ሐምዳን (ሐምዲቲ) ዳግሎ ሊሰራ ይሕ ቢቀር ይሰማ ይሆናል።በካርቱም የጦር ጄኔራሎችና በፖለቲካ ልሒቃን ዘንድ ያልተማሩ፣የግመል እረኛ፣ ደላላና የግመል ጋላቢዎች ሚሊሺያ አለቃ ተደርገዉ የሚታዩት ሐምዲቲ የተናቁትን አይነት ሰዉ እንዳልሆኑ በጦር ሜዳዉም በዲፕሎማሲዉም መስክ እያስመሰከሩ ነዉ።

ሁለቱ ጄኔራሎች በዲፕሎማሲዉ መስክ

10 ወር ባስቆጠረዉ ጦርነት ሐምዲቲ የሚመሩት ጦር ለሱዳን መከላከያ ኃይል በቀላሉ የማይደፈር እንደሆነ እያስመሰከረ ነዉ።ሰዉዬዉ ባለፉት ጥቂት ወራት ከዩጋንዳ እስከ ደቡብ አፍሪቃ ባደረጉት ጉብኝትና ዉይይት የአፍሪቃ መሪዎችን ድጋፍ ባያስገኝላቸዉ እንኳ ጠንካራ ተቃዉሞ አልገጠማቸዉም።ባለፈዉ ታሕሳስ አዲስ አበባ ዉስጥ የቀድሞዉ የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ከሚመሩት ከሱዳን የሲቢል ዴሞክራሲያዊ ኃይላት (ተቅዱም) ጋር ያደረጉት ስምምነት ደግሞ በሐገር ዉስጥ ያላቸዉን ተቀባይነት እያጎላዉ ነዉ።ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት ለሳላም ያደረጉት ጥሪ የሱዳናዉያንን አንጀት ያባባ፣የጠላቶቻቸዉን ቆሽት ያሳረረ ብጤ ሆኗል።

«ከዚሕ፣የሱዳን ሕዝብን በሙሉ ይቅርታ እንጠይቃለን።በሁሉም ግዛቶች ማለትም በምሥራቅ፣በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በደቡብና በመሐል በሁሉም ላይ ለተፈፀመዉ ጉዳት ሁሉ ይቅርታ እንጠይቃለን።ለሰላም እጃችንን እንዘረጋለን።ሰላም ከፈለጉ እንቀበላለን።ከሰላም ዉጪ ከኻርቱም የሚያስወጣት ኃይል የለም።»

ዳግሎ በቅርቡ ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ከሱዳን ተቃዋሚዎችና ከአፍሪቃዉያን መሪዎች ጋር ያግባባቸዉ ይመስላል
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎምስል Ashraf Shazly/AFP

የሱዳን ወታደራዊ መሪናየጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን አፀፋ ግን ሰዉዬዉ አሁንም እንደ ወታደር መዋጋት-ማዋጋት እንጂ እንደፖለቲከኛ የኃይል ሚዛንን ማነፃፀር፣ ወይም የዲፕሎማሲዉን ጥልፍልፍ መረዳት አለመቻላቸዉን መስካሪ ነዉ።አል ቡርሐን ከአዲስ አበባዉ መግለጫ ጥቂት ቀደም ብሎ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ድርድር ብሎ ነገር የለም።

«በየአካባቢዉ የሰፈረዉ የጦር ክፍል በሙሉ እነዚሕን አማፂያንንና ከሐዲዎችን ለማሸነፍ በጋራ መቆማቸዉን አረጋግጠዋል።ይሕንን ፈተናና ስቃይ ባጭር ጊዜ ለማስወገድ አስፈላጊዉን እርምጃ ሁሉ እንወስዳለን።»

ኢጋድ ሁለቱን መሪዎች ፊትለፊት ለማደራደር ከዚሕ ቀደም ይዞት የነበረዉን ቀጠሮም አል ቡርሐን አፍርሰዉታል።ኢጋድ ባለፈዉ ሐሙስ በጠራዉ ጉባኤ ላይ የፈጥኖ ደራሹ ጦር አዛዥን ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ መጋበዛቸዉን በመቃወም አል-ቡርሐን በጉባኤዉ አልተገኙም።ጉባኤዉ ከከኢጋድ አባል ሐገራት በተጨማሪ ሱዳን አባል የሆነችባቸዉ የአፍሪቃ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የዓረብ ሊግ ተወካዮች እንዲሁም የአዉሮጳ ሕብረት፣የዩናይትድ ስቴትስ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የሳዑዲ አረቢያና የሌሎችም መንግስታት ተወካዮች የተካፈሉበት ነበር።

አል ቡርሐን በዲፕሎማሲዉ መስክ ብዙም የቀናቸዉ አይመስልም
የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ምስል Sudanese Army/AFP

ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ግን በጉባኤዉ አለመካፈል አይደለም ሱዳንን ከመሰረተችዉ ኢጋድ አአባልነት እንድትወጣም ወስነዋል።አል ቡርሐን የሚመሩት የሱዳን መንግስት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ታስታጥቃለች በማለት የሚወቅሳት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን እርምጃዋን እንድታቆም የአረብ ሊግን ለመሳሰሉ አካባቢያዊ ማሕበራትና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቤቱታ ለማቅረብ ማቀዱን አስታዉቋል።የአል ቡርሐን አቋም፣ የመንግስታቸዉ ዉሳኔና ወቀሳ ተገቢና ትክክል ሊሆን ይቻላል፤ ግን ባንድ ጊዜ ከዉጪም፣ከዉስጥም ኃይላት ጋር እየተላተመ ከሚፈለገዉ ግብ ይደርስ ይሆን? ኢጋድስ ቢሆን፣ የሰላም ጥሪዉ ተገቢና ወቅታዊ ሊሆን ይችላል፤ ግን ከተፋላሚዎች አንዱ በሌለት ማንን-ከማን ጋር ሊያደራድር ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ